ተልእኮአችን
በከተማ አስተዳደሩ ብሎክን ማዕከል ያደረገ የአገልግሎት አሰጣጥ ፣ የመሠረተ ልማት ፣ የፀጥታ ችግሮችና የበጎ ፈቃድ ተግባራት ፍላጎቶችን በመለየት ፤ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማጎልበት ፤ ችግሮች ከምንጫቸው እንዲፈቱ በማድረግ የኅብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤
ራዕይ
በ2022 የለማ የኅብረተሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በጎ ፈቃድን ባህሉ ያደረገ ህብረተሰብ ተፈጥሮ ማየት፡፡
መመሥረት
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የከተማው ምክር ቤት የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ኮሚሽኑ በማዕከል ፣ በ11 ክፍለ ከተሞችና በ119 ወረዳዎች ተጠሪ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም በ4350 ብሎኮች የህብረተሰቡ ቀጥታ ወኪሎች የሆኑ የካውንስል አመራሮችን ያካተተ መዋቅራዊ አደረጃጀት ዘርግቷል፡፡
እሴቶች
- አሳታፊነት
- ሰብዓዊነት
- ፍትሐዊነት
- ተጠያቂነት
- በእውቀትና በእምነት መሥራት
- ለለውጥ ዝግጁነት
- ጥራትና ወጪ ቆጣቢነት
- ችግር ፈቺነት
ስልጣንና ተግባራት
- ብሎክን ማዕከል አድርጎ የተደራጀውን ሕብረተሰብ እና የህብረተሰብ ተሳትፎ ካውንስል አደረጃጀትን ቀጣይነት ባለው መልኩ ያደራጃል፣ ያጠናክራል፣ ይደግፋል፣ያስተባብራል፣ ክፍተቶች ሲኖሩ የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል፤
- በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰሩ ተግባራትን ይለያል፤ ተሳትፎ የሚጎለብትበትን ስልት ይቀይሳል፤ ስለህብረተሰብ ተሳትፎ አደረጃጀትና ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ ያስተዋውቃል፤
- የተቀናጀ የህብረተሰብ ተሳትፎ ውጤታማ እንዲሆን መመሪያዎች እና የአሰራር ሥርዓቶች ያዘጋጃል፤ ተግባራዊ ያደርጋል፤ አፈጻጸማቸውን ይከታተላል፤
- ህብረተሰቡ የብሎኩን የልማት ፍላጎት እንዲመለስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል፣ የሠላምና ፀጥታ፣ የሥራ አጥነት እና የማህበራዊ ችግሮች ለማስወገድ ነዋሪው በባለቤትነት እንዲደራጅ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፤
- አማራጭ የፋይናንስ ምንጮችን በመፈለግ አግባብ ባለው አካል ሲፈቀድ የአካባቢውን ህብረተሰብ የልማት ሥራ ያግዛል፤
- በብሎክ ነዋሪዎች የተለዩ ፍላጎቶች የሚሟሉበትን እና የተለዩ ችግሮች የሚፈቱበትን ዕቅድ ከብሎክ ካውንስል ጋር በመሆን ያዘጋጃል፤
- ከሚመለከታቸው የከተማው አስተዳደር አካላትጋር በመቀናጀት በብሎክ የተደራጁ ማህበረሰብ አቀፍ የህብረተሰብ ተሳትፎ ካውንስሎችን ችግሮቻቸው የሚፈቱበት እና ጥያቄዎቻቸው ምላሽ የሚያገኙበት ሁኔታ ያመቻቻል፤
- በብሎክ ውስጥ የተሰሩ ማንኛውም የልማት ሥራዎች በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውሉ እና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ ከብሎክ ካውንስል ጋር በመሆን ክትትል ያደርጋል፤
- በብሎክ በተምሳሌትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ሁለገብ የህብረተሰብ ተሳትፎ ያደረጉ እና የልማት ሥራዎችን ያከናወኑ ካውንስሎችን በመለየት እውቅና ይሰጣል ወይም እንዲሰጥ ያደርጋል፤
- የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በራስ መልካም ፈቃድ፣ ተነሳሽነት እና ያለማንም አስገዳጅነት ለሚሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል፤ ያስተባብራል፤ ይመራል፤
- በበጐ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰማሩ ወጣቶች፣ የሞያ ማህበራት፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተባብራል፣ የእውቅና እና ምስክር ወረቀት ይሰጣል፤
- ህብረተሰቡ ያለውን እውቀትና ችሎታ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ላይ እንዲያውልና ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችለውን የበጎ ፈቃድ ባህል እንዲያጎለብት ያበረታታል፤
- በከተማው የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በእቅዶቻቸውና በፕሮግራሞቻቸው ውስጥ አካትተው እንዲሰሩ ያደርጋል፤
- በከተማው ዘላቂ የበጐ ፍቃድ ፍኖተ ካርታ ያዘጋጃል፣ ምክር ቤት እንዲደራጅ ያደርጋል፤
- የከተማውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የከተማ ነዋሪ፣ የንግድ ድርጅቶች እና መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያደርጋል፤